Psalms 96

እግዚአብሔር፤ ንጉሥም ዳኛም

96፥1-13 ተጓ ምብ – 1ዜና 16፥23-33 1 ለእግዚአብሔር አዲስ ዝማሬ ዘምሩ፤
ምድር ሁሉ፤ ለእግዚአብሔር ዘምሩ።
2 ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ስሙንም ባርኩ፤
ማዳኑንም ነጋ ጠባ አውሩ።
3ክብሩን በሕዝቦች መካከል፣
ድንቅ ሥራውንም በሰዎች ሁሉ ፊት ተናገሩ።

4 እግዚአብሔር ታላቅ ነውና፤ ውዳሴም የሚገባው ነው፤
ከአማልክትም ሁሉ በላይ ሊፈራ ይገባዋል።
5የሕዝብ አማልክት ሁሉ ጣዖታት ናቸው፤
እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ።
6ክብርና ግርማ በፊቱ ናቸው፤
ብርታትና ውበትም በመቅደሱ ውስጥ አሉ።

7የሕዝቦች ወገኖች ሆይ፤ ለእግዚአብሔር ስጡ፤
ክብርንና ብርታትን ለእግዚአብሔር ስጡ።
8ለስሙ የሚገባ ክብርን ለእግዚአብሔር ስጡ፤
ቍርባንን ይዛችሁ ወደ አደባባዩ ግቡ።
9በተቀደሰ ውበት ለእግዚአብሔር ስገዱ፤
ምድር ሁሉ፤ በፊቱ ተንቀጥቀጡ።
10በሕዝቦች መካከል፣ “እግዚአብሔር ነገሠ” በሉ፤
ዓለም በጽኑ ተመሥርታለች፤ አትናወጥም፤
እርሱ ለሕዝቦች በእኩልነት ይፈርዳል።

11ሰማያት ደስ ይበላቸው፤ ምድርም ሐሤት ታድርግ፤
ባሕርና በውስጧ ያለው ሁሉ ያስተጋባ፤
12መስኩና በላዩ ያለው ሁሉ ይፈንጥዝ፤
ያን ጊዜ የዱር ዛፎች ሁሉ በደስታ ይዘምራሉ፤
13እርሱ ይመጣልና በእግዚአብሔር ፊት ይዘምራሉ፤
በምድር ላይ ሊፈርድ ይመጣል፤
በዓለም ላይ በጽድቅ፣
በሕዝቦችም ላይ በእውነት ይበይናል።
Copyright information for AmhNASV